ፕሮጀክቶችን ከመደበኛ የሥራ ሰዓት በተጨማሪ 24/7 ሰዓት መገንባት እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

ይህ የተገለፀው የሲዳማ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ባዘጋጀው አጠቃላይ የኮርፖሬሸኑ የሠራተኞች መድረክ ላይ ነው፡፡ የሲዳማ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዛሬ ህዳር 16/2018 ዓ.ም. አጠቃላይ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች የስብሰባ መድረክ አካሂዷል፡፡ በስብሰባው የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኤልያስ ቲሮ የኮርፖሬሽኑን የ2018 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ለሠራተኛዉ ያቀረቡ ሲሆን በሩብ ዓመቱ ባጋጠሙ ችግሮች፣ በሥራ አመራር ቦርድ በተቀመጡ አቅጣጫዎች እንዲሁም ከተሳታፊዎች በተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ ከስብሰባው ተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ዉይይት በማድረግ ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
 
ዋና ሥራ አስፈፃሚዉ አቶ ኤልያስ ቲሮ ፕሮጀክቶችን 24/7 ሰዓት መገንባት ሀገራዊ አቅጣጫ መሆኑን በመግለፅ ፕሮጀክቶችን በጥራትና በጊዜ ሠርቶ ማጠናቀቅ የህልዉና ጉዳይ በመሆኑ በአሁን ሰዓት ፕሮጀክቶችን በመደበኛ የስራ ሰዓት ብቻ መስራት የማያስኬድ መሆኑንና ከነባሩ በተለየ አግባብ ካልተሰራ ነባሩን የሥራ ባህል ይዞ ሀገሪቷን ለማሻገር የማይቻል በመሆኑ የሀገራዊ አቅጣጫዉን ተከትሎ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ዋና ስራ አስፈጻሚዉ በማብራራያቸዉም በተቋማችን በተለያዩ ፕሮጀክቶች የምሽት ሥራ ጅምሮች መኖራቸዉንና ይህንን አጠናክሮ በሁሉም ፕሮጀክቶች ማስቀጠል እንደሚገባ በመግለፅ ሥራው ከአሰሪና አማካሪ ጋር በጋራ የሚሰራ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ከነዚህ ባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከርና የጋራ በማድረግ ወደ ትግበራ መግባት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ለዚህም ምሽት ሊሰሩ የሚችሉ ሥራዎችን መለየትና በፈረቃ የሚሰሩ ቡድኖችን ማደራጀት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
 
ከትርፋማነት አንጻር ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በየአመቱ የሚደረጉ የሂሳብ ምርመራዎች ተቋሙ ትርፋማ መሆኑን ያረጋገጡ ሲሆን እየታየ ያለዉ ለዉጥ እና ዉጤታማነት የእያንዳንዱ ሠራተኛ የሥራ ዉጤት መሆኑንም ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም መንግስት ለሠራተኞች ያደረገዉን የደመወዝ ጭማሪ መነሻ በማድረግ ኮርፖሬሽኑ ለሠራተኛዉ የደመወዝ ጭማሪ ማድረጉንና በቦርድ የፀደቀ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ተቋሙ በክልሉ እየሠራ ባለዉ ሥራ በአጭር ጊዜ ዉስጥ መልካም ሥም መገንባት መቻሉን የገለፁት ዋና ሥራ አስፈፃሚዉ ይህንን መልካም ሥም አስጠብቆ ተቋሙን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ መስራት እንደሚገባና ለዚህም ፕሮጀክቶችን በጥራትና በጊዜ ማጠናቀቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
 
በማጠቃለያቸዉም ከመደበኛ የሥራ ሰዓት ዉጪ ፕሮጀክቶችን ከመገንባት ጎን ለጎን በቀጣይ የሥራ ላይ ስልጠናዎች በመስጠት ብቁ ባለሙያዎችን መፍጠር፣ ተቋሙ ያለዉን ዉስን ሀብት ፈጠራ በታከለበት ሁኔታ በቁጠባ በመጠቀምና የወጪ ቅነሳ ስትራቴጂ ተግባራዊ በማድረግ የሀብት ብክነትን መከላከል፣ የተሻለ ተሞክሮ ያላቸዉን ፕሮጀክቶች ልምድ በመቀመር ወደ ሌሎች ፕሮጀክቶች ማስፋት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰሩ የሚገባቸዉ ሥራዎች መሆናቸዉን አቅጣጫ በማስቀመጥ ዉይይቱ ተጠናቋል፡፡
ህዳር 16/2018 ዓ.ም.
ጥራት ላለው ግንባታ-ሲኮስኮ
 
 

Leave a Comment