የሩፎ ዋኤኖ ሞዴል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑ ተገለፀ፡፡

የሲዳማ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አለታ ጩኮ ወረዳ የሚገነባውን የአለታ ጩኮ ሩፎ ዋኤኖ ሞዴል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ህንጻ ግንባታ በተፋጠነ መልኩ እየገነባ እንደሚገኝ ተገለፀ፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከፌደራል ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በ554.3 ሚሊየን ብር የዉለታ ዋጋ በተቋራጭነት ዉል በመግባት ነሀሴ 25/2017 ዓ.ም ግንባታዉን የጀመረዉ ይህ የ2ኛ ደረጃ ት/ት ቤት ግንባታ ፕሮጀክት መንታ ጂ+2 ህንጻ፣ 4 ጥንድ የመማሪያ ብሎኮች፣ የአስተዳደር ህንጻዎች፣ የላብራቶሪ፣ ዎርክሾፕ፣ መጋዘን እንዲሁም የዘበኛ ቤት የያዘ ሲሆን በአጠቃላይ 19 ብሎክ እና 1 ጂ+2 ህንጻ ግንባታ ያካተተ ፕሮጀክት ነዉ፡፡
የፕሮጀክቱን ግንባታ በተመለከተ ለብሎኮች ህንጻ ግንባታ የሚሆኑ የፋዉንዴሽን ሥራዎች የተጠናቀቁ መሆኑንና የጂ+2 ህንጻ የመሰረት ቁፋሮ ስራ በመካሄድ ላይ መሆኑን የፕሮጀክቱ ኃላፊ ኢንጂነር ነብዩ ስዩም የገለፁ ሲሆን የአካባቢዉ መሬት ረግረጋማ መሆን እና ዉሃ አለመቻል እንዲሁም በፕሮጀክቱ የነበረዉ ከፍተኛ ዝናብ የፕሮጀክቱን ሥራ አስቸጋሪ አድርጎት እንደነበር አንስተዋል፡፡ በአሁን ሰዓት የዝናቡ ሁኔታ እየቀነሰ መሆኑ መልካም አጋጣሚ መሆኑን የገለፁት ኢንጂነር ነብዩ ፕሮጀክቱ የ1 አመት ፕሮጀክት መሆኑን በማስታወስ ለፕሮጀክቱ አስፈላጊ ማቴሪያሎች በወቅቱ እየቀረቡ በመሆኑ ፕሮጀክቱን በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እስከ ምሽት ስድስት ሰዓት ድረስ በፈረቃ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ኮርፖሬሽናችን ፕሮጀክቱን ከተያዘለት ጊዜ አስቀድሞ አጠናቆ በማስረከብ በአጭር ጊዜ ዉስጥ የአካባቢዉን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰራ ይሆናል፡፡
ጥቅምት 30/2018 ዓ.ም.
ጥራት ላለው ግንባታ-ሲኮስኮ

Leave a Comment