ሲዳማ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በሲዳማ ክልል በ335 ሚሊየን ብር የሚገነቡ 7 የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ለማካሄድ ውል ተፈራረመ።
ኮርፖሬሽናችን በሲዳማ ክልል ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ባለቤትነት በ335 ሚሊዮን ብር በሲዳማ ክልል 6 ወረዳዎች ላይ የሚገንቡ 7 የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን ግንባታ ለማካሄድ የሚያስችል የውል ስምምነት ከክልሉ መስኖ ልማት ኤጀንሲ ጋር ዛሬ መስከረም 27/2018 ዓ.ም. ተፈራርሟል። በክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ በተካሄደው የፊርማ ሥነ-ስርዓት ላይ ኮርፖሬሽናችን በተቋራጭነት የሲዳማ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ድርጅት በአማካሪነት ውል የፈፀሙ ሲሆን ኮርፖሬሽናችንን በመወከል የኮርፖሬሽናችን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤልያስ ቲሮ ከተከበሩ ኢንጂነር መስፍን በላይ የክልሉ መስኖ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ጋር ተፈራርመዋል፡፡
በዳሌ ፣ በሀዋሳ ዙሪያ ፣ በአለታ ጩኮ፣ በሻፋሞ እና በወ/ገነት ወረዳዎች የሚገነቡት 7ቱ ፕሮጀክቶች 500ሄክታር ማልማት የሚችሉ እና 984 አባወራዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ የሚጠበቅ ሲሆን ግንባታቸውም በ4 ወራት ዉስጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል።
በውል ስምምነቱ ወቅት የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢ/ር ከበደ ጋኖሌ በክልሉ የመስኖ ልማት ስራን ለማስፋፋት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች በመንደፍ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች ሥራ እየተተገበረ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን ከዚህ ቀደም በፕሮጀክቶች ግንባታ ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች በመለየትና በመፍታት ተግባራትን በትኩረትና በልዩ ዲሲፕሊን በመምራት ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ በጥራት ለማጠናቀቅ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የክልሉ የመስኖ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መስፍን በላይ የክልሉን ህዝብ የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና ግብርናን ለማዘመን የሚረዱ የመስኖ ፕሮጀክቶች በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለመገንባት የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ ዛሬ ስምምነት የተካሄደባቸው ፕሮጀክቶች አዲስ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙና ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም በሶላር እና የወንዝ ጠለፋ የሚሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኮርፖሬሽናችን ዋና ሥራ አስፈፃሚ እቶ ኤልያስ ቲሮ በበኩላቸው ቢሮው ከኮርፖሬሽኑ ጋር በጋራ በመስራት ኮርፖሬሽኑ እንዲጠናከር ለተቋሙ የጀርባ አጥንት በመሆኑ አመስግነው ፕሮጀክቶቹን በተያዘዉ የጊዜ ገደብ ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ኮርፖሬሽናቸው እንደሚሰራ ገልጸዋል።