የአለታ ወንዶና አለታ ጩኮ ከተማ የመጠጥ ውሃ ግንባታ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ግምገማና የመስክ ምልከታ ተደረገ።

የኢፌዴሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋማ በኮርፖሬሽናችን እየተገነቡ የሚገኙት የአለታ ወንዶ እና የአለታ ጩኮ ከተሞች ከፍተኛ የመጠጥ ውሃ ግንባታ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም በመስክ በመገኘት ምልከታ አድርገዋል። በመስክ ምልከታው የኮርፖሬሽናችን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኤልያስ ቲሮን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
 
ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋማ በጉብኝቱ ወቅት የሁለቱም የከተማ የመጠጥ ውሃ ግንባታ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን ገልፀዉ የማቴርያል አቅርቦትና የገንዘብ ፍሰቱ በተገቢው ሁኔታ ከተሳለጠ ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው ጊዜያት ለመጨረስ እንደሚቻልና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ፕሮጀክቶቹ በስኬት እንዲጠናቀቁ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ቃል ገብተዋል፡፡ ባለድርሻ አካላትም ለፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ የተለየ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸውና ሕብረተሰቡም በልማቱ ላይ ባለው አቅም ሁሉ ተሳታፊ እንዲሆን አሳስበዋል፡፡
 
የሲዳማ ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢ/ር ከበደ ጋኖሌ በበኩላቸው የሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች ከወሰን ማስከበር ጋር የሚነሱ ችግሮችን በፍጥነት በመፍታትና የማቺንግ ፈንድ መዋጮ በማጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
 
የኮርፖሬሽናችን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኤልያስ ቲሮ በበኩላቸው ፕሮጀክቶቹን በውል ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደሚሠሩና ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮች መፍትሄ ሊሰጣቸዉ እንደሚገባ ገልፀዋል።
የፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም በአሁን ሰዓት አለታ ወንዶ ፕሮጀክት 47.5% ላይ የሚገኝ ሲሆን በቅርቡ ግንባታው የተጀመረው አለታ ጩኮ ፕሮጀክት ደግሞ 13.6% አፈፃፀም ላይ ይገኛል።
 
ህዳር 26/2018 ዓ.ም
ጥራት ላለው ግንባታ-ሲኮስኮ
ፎቶ:የክልሉ ውሃ ቢሮ

Leave a Comment