Scwc News ኮርፖሬሽናችን የንፁህ መጠጥ ዉሃ ፕሮጀክት ለመገንባት የ571 ሚልዮን ብር ዉል ተፈራረመ፡፡ የሲዳማ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አለታ ጩኮ ከተማ በ571 ሚልዮን ብር የሚገነባውን የአለታ ጩኮ ከተማ የንፁህ መጠጥ ዉሃ ግንባታ ፕሮጀክት ለማከናወን ከሲዳማ ክልል ዉሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ጋር ዛሬ ዉል ተፈራርሟል፡፡ ኮርፖሬሽናችን ፕሮጀክቱን በተቋራጭነት ለመገንባት ዉል የገባ ሲሆን በሲዳማ ክልል ዉሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ በተደረገው የዉል መፈራረም ሥነ-ስርዓት ላይ ኮርፖሬሽኑን በመወከል የኮርፖሬሽናችን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤልያስ ቲሮ ከተከበሩ ኢንጂነር ከበደ ጋኖሌ የክልሉ ዉሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ጋር ቢሮዉን በመወከል ተፈራርመዋል፡፡በሲዳማ ክልል አለታ ጩኮ ከተማ የሚገነባዉና ከ82 ሺህ በላይ የአካባቢዉን ህብረተሰብ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የሚጠበቀዉ ይህ ፕሮጀክት ግንባታዉ በ15 ወራት ዉስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን የአካባቢዉን ህብረተሰብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር የሚቀርፍ መሆኑንም የክልሉ ዉሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር ከበደ ጋኖሌ ገልፀዋል፡፡የኮርፖሬሽናችን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤልያስ ቲሮ በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተሰጣቸውን ሀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸዉንና የፕሮጀክቱን ግንባታ በዉል ከተቀመጠው ጊዜ አስቀድሞ አጠናቆ በማስረከብ በአጭር ጊዜ ዉስጥ የአካባቢዉን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡ፕሮጀክቱ የ2000ሜ.ኩ ሪዘርቫየር ግንባታ፣ የ66ኪ.ሜ የቧንቧ ዝርጋታና ገጠማ፣ የዉሃ አገልግሎት ቢሮ ግንባታ፣ የጀነሬተር ቤት እና ሌሎች ተያያዥ ግንባታዎችንና የኤሌክትሮ መካኒካል ዕቃዎች አቅርቦትና ገጠማ ሥራዎችን ያካተተ ነው፡፡ሐምሌ 10/2017 ዓ.ምሲኮስኮ