ኮርፖሬሽናችን በሲዳማ ክልል አለታ ጩኮ ከተማ የሚገኘዉን የአለታ ጩኮ ከተማ ከፍተኛ የመጠጥ ዉሃ ግንባታ ፕሮጀክት እየገነባ ይገኛል፡፡

በፌደራል ዉሃ ሚኒስቴር ድጋፍና በክልሉ ዉሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ባለቤትነት በአለታ ጩኮ ከተማ በመገንባት ላይ የሚገኘዉ የአለታ ጩኮ ከተማ የመጠጥ ዉሃ ግንባታ ፕሮጀክት ከ82,000 በላይ የከተማዉን ህብረተሰብ የንፁህ መጠጥ ዉሃ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቅ ግዙፍ የመጠጥ ዉሃ ግንባታ ፕሮጀክት ሲሆን መነሻዉን በከተማዋ ከሚገኙ ሁለት ጥልቅ ጉድጓዶች የሚያደርገዉ ዉሃ ወደ ማጠራቀሚያ ገንዳዎች በመግባት ለህብረተሰቡ እንዲደርስ የሚደረግ ይሆናል፡፡

ኮርፖሬሽናችን በተቋራጭነት ዉል በመግባት እየገነባዉ የሚገኘዉና ግንባታዉ በመስከረም 5/2018 ዓ.ም የተጀመረዉ ይህ ፕሮጀክት የ2000ሜ.ኩ የኮንክሪት ሪዘርቫየር ግንባታ፣ የ66ኪ.ሜ የቧንቧ ዝርጋታና ገጠማ፣ የዉሃ አገልግሎት ቢሮ ግንባታ፣ የቦኖዎች፣ የጀነሬተር ቤት፣3 የመፀዳጃ ቤት እና ሴፕቲክ ታንክ እና ሌሎች ተያያዥ ግንባታዎችንና የኤሌክትሮ መካኒካል ዕቃዎች አቅርቦትና ገጠማ ሥራዎችን ያካተተ ሲሆን የ15 ወራት የግንባታ ጊዜም ተይዞለታል፡፡
የፕሮጀክቱ ሃላፊ ኢንጂነር ሲሳይ ሃሜሶ የፕሮጀክቱን አፈፃፀም በተመለከተ በሰጡት ገለፃ በአሁን ሰዓት የዉሃ አገልግሎት ህንጻ ግንባታ እንዲሁም በተለያየ ሳይት የሚገኙ 3 የመፀዳጃ ቤት፣ የሴፕቲንክ ታንክ እና ሶክ አዌይ ፒት ግንባታ በመከናወን ላይ መሆኑን ገለፀዉ ለመስመር ዝርጋታ ስራዉም 12ኪ.ሜ. የቁፋሮ ስራ መከናወኑን ገልፀዋል፡፡ ከዉሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ግንባታ ጋር በተያያዘ ለግንባታዉ የሚያስፈልጉ ግብአቶች ብረትን ጨምሮ የማዘጋጀት ስራ መሰራቱን ሆኖም የማጠራቀሚየ ገንዳዉ ወደሚገነባበት ቦታ የሚወስደዉ መግቢያ መንገድ በከተማዉ አስተዳደር በኩል ያልተመቻቸ በመሆኑ የግንባታ ስራዉን መጀመር አለመቻሉን አንስተዋል፡፡ ኮርፖሬሽናችን ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ዉስጥ አጠናቆ ለማስረከብ የሚሰራ ሲሆን የከተማ አሰተዳደሩም ከመግቢያ መንገድ ጋር በተያያዘ ላለዉ ችግር አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ህዳር 4/2018 ዓ.ም.
ጥራት ላለው ግንባታ-ሲኮስኮ

Leave a Comment