የኮርፖሬሽናችን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤልያስ ቲሮ ከዘርፍ ሃላፊዎችና ማኔጅመንት አባላት ጋር በመሆን ኮርፖሬሽኑ እየገነባቸዉ በሚገኙ ፕሮጀክቶች የመስክ ምልከታና ግምገማ አከናዉነዋል፡፡ የመስክ ምልከታዉም በወንዶ ገነት ከተማ በመገንባት ላይ ያሉ የወንዶ ገነት ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት፣ የወንዶ ገነት ከንቲባ ጽ/ቤት ጂ+4 ህንጻ፣ የወንዶገነት ሴክተር መ/ቤቶች ቢ+ጂ+3 ህንጻ ግንባታ ፕሮጀክቶች፣ የለኩ ኢንደስትሪ ፓርክ ሼድ ግንባታ፣ የአለታ ወንዶ ከተማ የመጠጥ ዉሃ ግንባታ፣ የአለታ ጩኮ ከተማ መጠጥ ዉሃ ግንባታ እንዲሁም የሩፎ ዋኤኖ አለታ ጩኮ ሞዴል 2ኛ ደረጃ ት/ት ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች የተደረገ ሲሆን ፕሮጀክቶች ያሉበት አሁናዊ የአፈፃፀም ደረጃም ተገምግሟል፡፡ በጉብኝቱም ወቅት የወንዶ ገነት ከተማ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የሬድ አሽ በቂ ምርት ገበያ ላይ ማግኘት አለመቻል ስራዉን በተፈለገዉ ፍጥነት ለማስኬድ እንቅፋት መሆኑን በአለታ ወንዶ መጠጥ ዉሃ ፕሮጀክትም የመስመር ዝርጋታ ስራ በወሰን ማስከበር ምክንያት የዘገየ ቢሆንም አሁን ላይ በተወሰነ መልኩ ችግሩ በመፈታቱ የዝርጋታ ስራዉ መጀመሩን የፕሮጀክቶቹ ሃላፊዎች አስረድተዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚዉ በጉብኝታቸዉ ወቅት የፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም ጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን በማንሳት ፕሮጀክቶቹን ፈጥኖ በማጠናቀቅ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የፈረቃና የምሽት ስራ ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የገለፁ ሲሆን አስፈላጊ የግብአት አቅርቦቶች በዋናዉ ቢሮ በኩል ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡ አያይዘዉም የዲዛይን ማሻሻያና የለዉጥ ስራ ትዕዛዝ የሚፈልጉ ስራዎችን እንዲሁም የወሰን ማስከበር ችግሮችን ከአማካሪ እና አሰሪ ተቋማት ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ ክትትላችንን አጠናክረን ሌሎች በእጃችን ያሉ መስራት የምንችላቸዉን ስራዎች ትኩረት ሰጥተን መስራት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ህዳር 3/2018 ዓ.ም.
ጥራት ላለው ግንባታ-ሲኮስኮ