የሲዳማ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የበላይ ሥራ አመራር ቦርድ የተለያዩ ዉሳኔዎችን አሳለፈ፡፡
የሲዳማ ኮንስትራክሽን ሥራዎች የሥራ አመራር ቦርድ ዛሬ ህዳር 10/2018 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሞ ያፀደቀ ሲሆን በአዲሱ የሠራተኞች ደመዎዝ ጭማሪ እና የተሸከርካሪ ግዥ ላይም ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የኮርፖሬሽኑን የ2018 በጀት ዓመት ሪፖርት ያቀረቡት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኤልያስ ቲሮ ኮርፖሬሽኑ በ2018 በጀት ዓመት በመስኖ፣ በመጠጥ ዉሃ፣ በጉድጓድ ቁፋሮ እና በህንፃ ግንባታ ዘርፍ ከ3.8ቢሊየን ብር በላይ የዉለታ ዋጋ ያላቸዉ 39 ፕሮጀክቶችን ይዞ ሲገነባ የቆየ ሲሆን ከዚህ ዉስጥ 19ኙ በሩብ ዓመቱ የተገኙ አዲስ ፕሮጀክቶች መሆናቸዉን ተናግረዋል፡፡ በገለፃቸዉም በሩብ አመቱ 7 ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ መቻሉን እንዲሁም ለ7770 ዜጎች በፕሮጀክቶች ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠሩንም አስረድተዋል፡፡
የኮርፖሬሽኑን ሥራ አመራር ቦርድም በቀረበዉ ሪፖርት መነሻ የኮርፖሬሽኑ አፈፃፀም እያደገና በየጊዜዉ የሚታይ ግልፅ ለዉጥ እያመጣ የሚገኝ መሆኑን በመግለፅ ከፕሮጀክቶች የሥራ ባህል ጋር በተያያዘ በመሶብ ፕሮጀክት የታየዉ አይነት አፈፃፀም እንዲሁም በተቋሙ የተጀመረው የምሽት ሥራ በሌሎች ፕሮጀክቶችም ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ እንደኮሪደር ልማት ባሉ ሥራዎች መሳተፍ መጀመሩ እንዲሁም ከፌደራል ተቋማት ጋር መስራት መጀመሩ ጥሩ ጅምር መሆኑን በማንሳት በቀጣይ ሥራዎችን ከክልል ዉጪ ጭምር በመስራት ተቋሙ ተወዳዳሪ ሆኖ መዉጣት እንዳለበት አስገንዝቧል፡፡
የሥራ አመራር ቦርዱ ሠብሳቢ የተከበሩ አቶ አሸናፊ ኤልያስ በበኩላቸዉ ኮርፖሬሽኑ በክልሉ ሠፊ ሥራ መስራቱንና ከልማት ጋር የተያያዙ ብዙ ችግሮችን መፍታቱን በማንሳት ኮርፖሬሽኑ ፕሮጀከቶችን በዉል ጊዜ ዉስጥ አጠናቆ በመጨረስ በጊዜ እና በጥራት ተወዳዳሪ ተቋም ሆኖ መዉጣት እንዳለበት በተጨማሪ ከተቋሙ ጋር የሚሄዱ ተቋሙን በግብአት ሊያግዙ የሚችሉ ተጨማሪ የገቢ ማግኛ ተቋማት በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት ቢቻል መልካም መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በአጠቃላይ ቦርዱ ኮርፖሬሽኑ እያሳየ ያለዉ የሥራ አፈፃፀም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን በማሳሰብ የቀረበዉን ሪፖርት በሙሉ ድምፅ አጽድቋል፡፡
በመቀጠልም አዲሱን የመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ ተከትሎ በኮርፖሬሽኑ ተዘጋጅቶ ለሥራ አመራር ቦርዱ ለዉይይት የቀረበዉ የሠራተኛ ደመወዝ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ሰፊ ዉይይት ተድርጎ ተፈፃሚ እንዲሆን በሥራ አመራር ቦርዱ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል፡፡ በመጨረሻም ኮርፖሬሽኑ ካለዉ የሥራ ስፋት አንፃር የሚታዩ የተሸከርካሪ እጥረቶችን ለመቅረፍ ከዚህ ቀደም 4 ገልባጭ ተሽከርካሪዎችን በራስ አቅም መግዛቱ የሚታወስ ሲሆን ለሥራ አመራር ቦርዱ የቀረበዉ ተጨማሪ የ4 ገልባጭ እና የ1 ፍላት ተሸከርካሪ ግዥም በቦርዱ ፀድቆ ስብሰባዉ ተጠናቋል፡፡
ህዳር 10/2018 ዓ.ም.
ጥራት ላለው ግንባታ-ሲኮስኮ