Scwc News የሲዳማ ብሄራዊ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ የጎርቼ ሆስፒታል እና የደራራ ጤና ጣቢያ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ፡፡ የሲዳማ ብሄራዊ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ሠላማዊት መንገሻ ከተለያዩ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ኮርፖሬሽናችን በሲዳማ ክልል ጎርቼ ወረዳ እየገነባ የሚገኘዉን የጎርቼ B+G+2 ሆስፒታል ግንባታ እንዲሁም የደራራ ወረዳ የጤና ጣቢያ ግንባታ ፕሮጀክቶች በመገኘት የመስክ ምልከታና ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በጉብኝቱም ከዋና ቢሮ ሃላፊዋ በተጨማሪ የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይነህ በቀለ፣ የክልሉ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር መብራቴ መለሰ እና ምክትል ዳይሬክተር ኢንጂነር ጎንሳሞ ጉሳ ፣ የዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር መላኩ ገ/መስቀል፣ የኮርፖሬሽናችን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኤልያስ ቲሮ እንዲሁም የክልሉ ጤና ቢሮ እና የክልሉ የዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ድርጅት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ በመስክ ምልከታው ወቅት ፕሮጀክቶቹ ያሉበትን የአፈጻጸም ደረጃ የፕሮጀክቱ ሃላፊ ኢንጂነር መሀመድ አሊ ለጉብኝዎች ያብራሩ ሲሆን የጉብኝቱ ተሳታፊዎች በፕሮጀክቶቹ ግንባታ ባዩት የሥራ ጥራት መደሰታቸውንም ገልፀዋል፡፡ የደራራ ጤና ጣቢያ በተመለከተ ተጨማሪ የሚሰሩ ስራዎች የውለታ ሰነድ አካል ተደርገዉ ለኮርፖሬሽኑ በአስቸኳይ እንዲሰጡና በፍጥነት ተሰርተው ፕሮጀክቱ ለርክክብ እንዲደርስ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን የጎርቼ ሆስፒታል ግንባታም አሁን ባለው ፍጥነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ተቀምጧል። የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሠላማዊት መንገሻ በኮርፖሬሽኑ የተነሳው የክፍያ መዘግየት ችግር ለመፍታት ከሚመለከተው የመንግስት መዋቅር ጋር በመነጋገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመክፈል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን በመጥቀስ ኮርፖሬሽኑ ያሉትን ችግሮች ተቋቁሞ በሰራቸው ስራዎች እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን በመግለፅ የመስክ ምልከታውን አጠናቀዋል። #ሲኮስኮህዳር 26/2018 ዓ.ም.ጥራት ላለው ግንባታ-ሲኮስኮ