ኮርፖሬሽናችን በሲዳማ ክልል አለታ ጩኮ ከተማ በመገንባት ላይ የሚገኘዉን የሩፎ ዋኤኖ አለታ ጩኮ ሞዴል 2ኛ ደረጃ ት/ት ቤት የግንባታ ሂደት የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ የተከበሩ አቶ በየነ በራሣ ከኮርፖሬሽናችን ዋና ሥራ አስፈፃሚና ሌሎች አመራሮች ጋር በመሆን ዛሬ ህዳር 9/2018 ዓ.ም. የመስክ ምልከታና ጉብኝት አካሂደዋል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት የፕሮጀክቱ ሃላፊ ኢንጂነር ነብዩ ስዩም ለፕሮጀክቱ ሥራ ከፍተኛ ማነቆ የነበረዉ በአካባቢዉ የነበረዉ ዝናብ በአሁን ሰዓት የቀነሰ በመሆኑ የተሻለ የግንባታ ሁኔታ መፈጠሩን በመጥቀስ ቀጣይ የዝናብ ወቅት ሳይደርስ አሁን ያለዉን ምቹ ሁኔታ በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ በመሆኑና በዝናብ ምክንያት የተስተጓጎለዉን የግንባታ ጊዜ ለማካካስ በፕሮጀክቱ በአሁን ሰዓት በፈረቃ ምሽት ጭምር ግንባታዉ እየተካሄደ የሚገኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመስክ ምልከታዉም የተከበሩ አቶ በየነ በራሣ ፕሮጀክቱ ለአካባቢዉ ህብረተሰብ ብሎም ለክልሉ ህዝብ የሚሰጠዉ ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን በማስታወስ በፕሮጀክቱ ባዩት የግንባታ ሂደትና ፍጥነት መደሰታቸዉን የገለፁ ሲሆን የፕሮጀክቱ ፍጥነት አሁን ባለዉ ሁኔታ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የኮርፖሬሽናችን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኤልያስ ቲሮ በበኩላቸዉ ኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቱን በዉል ጊዜ አጠናቆ ለማስረከብ ቁርጠኛ መሆኑን በማንሳት ለዚህም አሁን ያለዉ የግንባታ ሂደት እና ፍጥነት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
ሩፎ ዋኤኖ ሞዴል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በፌደራል መንግስት ወጪ በፌደራል ት/ት ሚኒስቴር አሰሪነት በሲዳማ ክልል በመገንባት ላይ የሚገኝ ፕሮጀክት ሲሆን የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ለአካባቢዉ ህብረተሰብ የትምህርት ሽፋን በማዳረስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይጠበቃል፡፡
ህዳር 9/2018 ዓ.ም.
ጥራት ላለው ግንባታ-ሲኮስኮ